1 Chronicles 28

ዳዊት ስለ ቤተ መቅደሱ ያወጣው ዕቅድ

1ዳዊት በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የነገዱን የጦር አለቆች፣ ንጉሡን የሚያገለግሉትን የከፍለ ጦር አዛዦች፣ የሻለቆቹን፣ የመቶ አለቆቹን፣ የንጉሡና የልጆቹ ንብረትና ከብት ሁሉ ኀላፊ የሆኑትን፣ እንዲሁም የቤተ መንግሥቱን ሹማምት፣ ኀያላንና ጀግና ተዋጊዎቹን፣ በአጠቃላይ የእስራኤልን ሹማምት ሁሉ ጠራ።

2ከዚያም ንጉሥ ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞቼና ወገኖቼ ሆይ፤ እስቲ አድምጡኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦት ማደሪያና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን ቤት ለመሥራት ዐስቤ ዕቅድ አውጥቼ ነበር። 3እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘ጦረኛ ሰው ስለ ሆንህና ደምም ስላፈሰስህ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራም።’

4“ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንድነግሥ ከቤተ ሰቤ ሁሉ እኔን መረጠ፤ መሪ እንዲሆንም ይሁዳን መረጠ፤ ከይሁዳም ቤት የእኔን ቤተ ሰብ መረጠ፤ ከአባቴ ልጆች መካከል ደግሞ በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ ፈቃዱ ሆነ። 5እግዚአብሔር ብዙ ልጆች ሰጥቶኛል፤ ከወንዶቹ ልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ደግሞ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። 6እንዲህም አለኝ፤ ‘ቤቴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ ምክንያቱም ልጄ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ። 7አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምንጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ’።

8“እንግዲህ አሁንም ይህችን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሷቸው፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዝዛችኋለሁ።

9“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል። 10ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።”

11ከዚያም ዳዊት የቤተ መቅደሱን መመላለሻ፣ የሕንጻውን፣ የዕቃ ቤቶቹን፣ የፎቁንና የውስጥ ክፍሎቹን እንዲሁም የማስተስረያውን ቦታ ንድፍ ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። 12ደግሞም መንፈስ ቅዱስ በልቡ ያሳደረውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አደባባይ፣ በዙሪያው ያሉትን ክፍሎች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶችና የንዋየ ቅድሳቱን ግምጃ ቤቶች ንድፍ ሁሉ ሰጠው፤ 13እንዲሁም የካህናቱንና የሌዋውያኑን አመዳደብ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራና ለአገልግሎቱ ስለሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ሁሉ መመሪያ ሰጠው። 14ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ መጠን፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የብር ዕቃዎች ሁሉ መጠን አሳወቀው፤ 15እንደየመቅረዙ አገልግሎት ዐይነት ለወርቁ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚሆነውን የእያንዳንዳቸውን የወርቅ መጠን፣ ለብሩ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚያስፈልገውን የእያንዳንዳቸውን የብር መጠን፣ 16ለእያንዳንዱ፣ ገጸ ኅብስት ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱም የብር ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣ 17ለሹካዎቹ፣ ለጐድጓዳ ሳሕኖቹ፣ ለማንቈርቈርያዎቹ የሚያስፈልገውን ንጹሕ የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱ የብር ሳሕን የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣ 18ለዕጣኑ መሠዊያ የሚሆነውን የጠራ ወርቅ መጠን እንዲሁም ክንፎቻቸውን ዘርግተው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸፍኑትን ከወርቅ የተሠሩትን የኪሩቤል ሠረገሎች ንድፍ ሰጠው። 19ዳዊትም፣ “ይህ ሁሉ፣ በእኔ ላይ ባለው በእግዚአብሔር እጅ በጽሑፍ ተገለጠልኝ፤ የንድፉንም ዝርዝር እንድረዳ ማስተዋልን ሰጠኝ” አለ።

20ደግሞም ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋር ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም። 21ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ሁሉ የሚያስፈልጉት ካህናትና ሌዋውያን ምድብም ዝግጁ ነው። በሁሉም የእጅ ሙያ የሠለጠኑ ፈቃደኛ ሰዎች በሥራው ሁሉ ይረዱሃል። ሹማምቱና ሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝህን ይፈጽማሉ።”

Copyright information for AmhNASV